Connect with us

Uncategorized

ትግራይ ላይ የሚካሄደው ጦርነት በሌላ ኢትዮጵያዊት ዓይን (ክፍል 3፥ የመጨረሻ)

ባለቤቴ እና አንድ የአ.አ ልጅ ትግሬ አሉ። ሁዋላ ላይ ሲነግሩን አብረውን የመጡት ራሱ አማራ ነው ያሉት ለካ። ከዛ የእኔን ባለቤት እና ያንን ልጅ እናንተ አታልፉም ሌሎቻችሁ መሄድ ትችላላችሁ አለ ብሄር የጠየቀን ፖሊስ። ላዋራው ስቀርበው አትጠጊኝ ሂጂ ሂጂ አለኝ።

Published

on


የፀሐፊዋ መግቢያ (ስሟ ሊገለፅ ኣልፈለገችም)፦ ትግራይ ውስጥ ለ1 አመት ከ8ወር ኖሬአለሁ። ጦርነቱ ከመታወጁ በፊት ህይወት መልካም ነበር። ማንም ሰው ይሄ እንዲገጥመው አልመኝም። ጦርነቱ ከተጀመረ ለ20 ቀናት የገፈቱ ቀማሽ የችግሩም ተቋዳሽ ነበርኩ። ሌሎቹ ክፍሎች፡ ክፍል 1 እና ክፍል


ሰርዶ እንደደረስን ሁላችሁም ውረዱ ተባልን። ፌዴራል እና መከላከያ ተቀላቅለው ነበር። ከዛ ከመሀከላቸው አንዱ እየዞረ ብሄር መጠየቅ ጀመረ። ክፉ አላሰብንም። ባለቤቴ እና አንድ የአ.አ ልጅ ትግሬ አሉ። ሁዋላ ላይ ሲነግሩን አብረውን የመጡት ራሱ አማራ ነው ያሉት ለካ። ከዛ የእኔን ባለቤት እና ያንን ልጅ እናንተ አታልፉም ሌሎቻችሁ መሄድ ትችላላችሁ አለ ብሄር የጠየቀን ፖሊስ። ላዋራው ስቀርበው አትጠጊኝ ሂጂ ሂጂ አለኝ። ያ መከረኛ እምባዬ መፍሰስ ጀመረ።

እውነት ለመናገር ብዙዎቹ አዝነውልኛል። ያ ፖሊስ ግን ጠመመ። እቃችንን አውርዱ ተባልን። ገንዘባችን ተመለሰ። እልም ያለ በረሀ ነው። ወደ አብአላ ይመለሱ ፤ መኪና ይዘጋጅላቸው ማለት ጀመረ። እንባዬን ያዩት ሌሎቹ ግን ይሞግቱት ጀመር። እሱ ግን ስልክ ይደውላል፤ ከአለቃው ጋር ይመስለኛል ትግሬ እንዳታሳልፉ ብለህ የለ እያለ ይከራከራል ። አለቃውም ይሂዱ ቢለውም እሱ ግን ሊለቀን አልፈለገም።

እግዚአብሔር ያክብራቸውና እየመጡ ብዙዎቹ ፖሊሶች እየመጡ አፅናኑን። በተለይ አንደኛው ቃል እገባላችሇለሁ አትለያዩም አለን። ፀሀዩ አቀለጠን። ቢያንስ 2 ሰአት ያህል ቆመናል። በመጨረሻም እቃችንን ያዙ ተባልን። በፒክ አፕ መኪና ወደ ሰመራ እንደምንሄድ ተነገረን። ሰመራ ለምን እንደምንሄድ ያን ደግ ፖሊስ ጠየቅሁት። ብዙም ማውራት አልፈለገም። እዛ ስትሄዱ ይነግሯችኋል አለኝ። መልሱ ቢያደናግረኝም መኪናው ውስጥ ገባን። አጃቢ ፓሊስ ተመድቦልን ጉዞ ጀመርን። ቢያንስ ቢያንስ ወደ አብአላ አልመለሱንም ብዬ ተፅናናሁ።

ሰመራ ስንደርስ ሰርዶ ላይ ትቶን የመጣው መኪናችንን አየነው። የከተማው መግቢያ አካባቢ ወዳለው ፖሊስ ኮሚሽን ይዘውን ገቡ። አብረውን የመጡት ልጆች በሙሉ አሉ። አንድ ፖሊስ ስም እየጠራ ይመዘግባል። ከዛ ለባለቤቴ እና ለአ.አው ልጅ ብሄር ሲጠየቁ አማራ እንዲሉ ነገርኳቸው። ከዛ በሁዋላ ሁላችንም ያለ ፖሊሶቹ ፍቃድ መንቀሳቀስ እንደማንችል ሽንት ቤት እንኳን አስፈቅደን መሄድ እንዳለብን ነገሩን። ገንዘብ ስለሌለን ባንክ እንድንሄድ ስንጠይቃቸው 10 ሰው ብቻ መሄድ እንደሚችል እሱም ከአጃቢ ፖሊስ ጋር እንደምንሄድ ነገሩን። ባንክ ብንሄድም የትግራይ ክልል አካውንት እንደማይሰራ ነገሩን። በሌላ አካውንት ስንሞክር ደሞ ኔትወርከ ጠፋ። ተስፋ ቆርጠን ተመለስን። ምግብ ጠዋት የቀመስን ነን።

እየመሸ ሲሄድ ግራ መጋባት ጀመርን። መቼ ነው ምንሄደው ስንላቸው ዛሬ ትሄዳላችሁ ይሉናል…መጨለም ጀመረ። ከዛ መውጣት እንደማንችል እና እዛው አፈሩ ላይ እንድንተኛ ነገሩን። እኔ እና ባለቤቴ አፈር ላይ መተኛት እንደማልችል በዛ ላይ እንደታመምኩ ነገርናቸው። መታወቂያ እና ፓስፖርት ተቀበሉን። አሁንም በሁለት መሳሪያ በታጠቁ ፖሊሶች ወደ ሆቴል አደረሱን እና በጠዋት እንድንመጣ ነገሩን። አልገባንም እንጂ ለካ እስር ቤት እየገባን ነው። ጠዋት ተመልሰን ሄድን። ሰውነቴ እብጠቱ እየጨመረ ወገቤን በጣም እየተሰማኝ ነበር። አሁንም እንደ ትናንትናው ትሄዳላችሁ ይሉናል ። ግን እዛው ቀረን። በዛ ላይ እዛ እንደ እኛ ገብተው ከ3ቀን በላይ የቆዩ ሰዎች ሠኖራቸውን አስተዋልን። በእዚህ ጊዜ ባለቤቴ ለቤተሰቦቼ መደወል ጀመረ። አፋር መሆናችንን ሲሰሙ እጅግ በጣም ደነገጡ። በአጋጣሚ አንድ ከፍተኛ የአፋር ባለስልጣን ስለሚያውቁ ደወሉለት። እሱ ደግሞ ለሃላፊዎቹ ነብሰ ጡር እንደሆንኩ ባለቤቴም ሰላማዊ ዜጋ እንደሆነ ለሚፈጠር ነገርም ሀላፊነት እንደሚወስድ ነገራቸው። ቀን 10 ሰአት አካባቢ ለቀቁን። ወደ አ.አ ለመሄድ የባለቤቴ መታወቂያ አስፈራን። የእኔ ቤተሰቦች ባህር ዳርም ስላሉ በሎጊያ አድርገን አማራ ክልል ለመግባት ወሰንን። ቤተሰቦቼም ኮምቦልቻ መኪና እንደሚጠብቀን ነገሩን። ይሄ ነው የማይባል ችግር ሳይፈጠር ባህር ዳር ገባን።

አሁን የሴት ልጅ እናት ሆኛለሁ። ለልጄ የምነግራት ታሪክ ግን ያስፈራኛል። ብዙ ሰው ህወሀት ያመጣብን ጣጣ ነው ምንም ማድረግ አይቻልም ይላል። ግን እንዴት ብዬ ነው አንቺ ስትወለጂ አባትሽ የተወለደበት ከተማ ፈራርሶ ነበር፤ አያትሽ አክስቶችሽ አጎቶችሽ በረሀብ ደቀው የሰው እጅ ይጠብቁ ነበር፤ አያትሽ አክስቶችሽ እንዳይደፈሩ ቀን በረሀ ላይ እየዋሉ ማታ መመለሳቸውን እንዴት ነው ምነግራት?!

የት መኖር እንዳለብን አላውቅም፤ ህይወት ከብዶናል፤ ከእዚህ ሀገር መውጣት ነው ምንፈልገው፤ እኔን ግን የሚገርመኝ እርስ በእርስ ተሳስረን ተጋምደን ይሄ ሁሉ ጥላቻ ከየት መጣ?! ባልመረጥነው ዘራችን ምክንያት ብዙ ተገፍተናል። ዛሬ የትግራይ ወገንህ ላይ እለት እለት የሚደርሰው ስቆቃ እና ግፍ አንተ ባይሰማህ ከእነሱም ልብ ኢትዮጵያዊነት እየተፋቀ መሆኑን አትዘንጋ። የግድ ለሰው ለማዘን ችግር ቤትህን ማንኳኳት የለበትም። እግዚአብሔር ልብ ይስጠን። እግዚአብሔር እኛን ከእዚ እንዳወጣን ለተጨነቃችሁ ፈጣሪ ይድረስላችሁ።

Continue Reading
Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.